Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ጅቡቲ የመረጃ ተቋማት በድንበር አካባቢ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ )የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የጅቡቲ የመረጃ ተቋም በድንበር አካባቢ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፥ በጅቡቲ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ሐሰን ሰይድ የተመራ ከሀገሪቱ የጸጥታና ደኅንነት አካላት የተወጣጣ የልዑካን ቡድን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ጎብኝቷል፡፡

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላና ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን፥ ከጉብኝቱ ጎን ለጎን ልዑኩ እና የኢትዮጵያ አቻ ተቋማት የተካፈሉበት የሁለትዮሽ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ሁለቱ ሀገራትም በድንበር እንዲሁም በቀጣናው በሚስተዋሉ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚያከናውኗቸውን ስምሪቶች አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ባሻገር በጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የተሳሰሩ ሀገራት እንደመሆናቸው የጋራ የጸጥታና የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸው በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡

በተለይ ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ ሕገወጥ የገንዘብ፣ የመሣሪያና የሰዎች ዝውውር የጋራ የጸጥታ ሥጋት በመሆናቸው፤ ችግሮችን ለማስቀረት የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያና የጅቡቲ የመረጃና የጸጥታ አካላት በሁለቱ ሀገራት የድንበር አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን እና ሕገወጥ ታጣቂዎችን ለመከላከል በጋራ የሚሠሩትን ተግባር ለማጠናከር መስማማታቸውን የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ ያስረዳል፡፡

ውይይቱ በድንበርም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጿል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ደኅንነትና እጣ ፈንታ እጅጉን የተሳሰረ በመሆኑ የጅቡቲ መጠቃት በኢትዮጵያ ላይ እንደደረሰ እንደሚቆጠር በኢትዮጵያም የሚፈጸም ጥቃት ጅቡቲን እንደሚመለከት በውይይት መድረኩ ተነስቷል ነው ያለው፡፡

በዚህ መነሻነትም ጅቡቲ ከየትኛውም አካል የሚፈጸምባትን ትንኮሳና የሚያጋጥማትን የደኅንነት ሥጋት ለመቀልበስ ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጎን እንደምትቆም ተጠቅሷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ እንደጠቆመው በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት የመረጃና የጸጥታ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተካፍለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.