Fana: At a Speed of Life!

ወጣቶች በሚጓዙባቸው የአፍሪካ ሀገራት ቋሚ ወንድማማችነትን መትከል አለባቸው- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ዲፕሎማሲ ወጣቶቿ በሚጓዙባቸው የአፍሪካ ሀገራት ቋሚ ወንድማማችነትን መትከል እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ወደተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሽኝት ተደረጎላቸዋል፡፡

ወጣቶቹ ጉዞ በሚያደርጉባቸው ሰባት የአፍሪካ ሀገራት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደሚያከናውኑም ነው የተገለጸው፡፡

በመርሐ ግብሩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለበጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ፥ ወጣቶች በሚጓዙባቸው የአፍሪካ ሀገራት ቋሚ ወንድማማችነትን መትከል እንዳለባቸው ነው ያነሱት፡፡

ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰችበት ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የማስፋትና ወንድማማችነትን የማኖር ዓላማንም ያከናውናሉ ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ በኋለኛው ዘመን የአፍሪካ የነፃነት መሪ፣ ዛሬ በሰላም ማስከበር የገዘፈ ሚናዋ የምንኮራባት ሀገር ናት ብለው፥ የኢትዮጵያ ነፃነት ተምሳሌትነት የፓን አፍሪካን አሻራ በአረንጓዴ አሻራ ማስቀጠል ሌላው ተልእኮ ነውም ብለዋል፡፡

የአፍሪካን ወንድማማችነት በመትከል መርሐ ግብር ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በጎረቤት የአፍሪካ ሀገራት የችግኝ ተከላ፣ ውይይት እና ጉብኝት ያደርጋሉም ነው የተባለው።

100 የሚሆኑት ወጣቶችም ከነገ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱማሊያ፣ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ እና ሩዋንዳ የችግኝ ተከላና ወንድማማችነትን ይተክላሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በፀጋዬ ወንድወሰን

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.