የሀገር ባለውለታ ለሆኑ አረጋውያን ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል-ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር ባለውለታ ለሆኑ አረጋውያን ተገቢውን ትኩረት፣ ክብር፣ ድጋፍና እንክብካቤ መስጠት ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡
የዘንድሮው የአረጋውያን ቀን “የአረጋውያን ኢትዮጵያዊነት አሻራ ለትውልድ አደራ” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ31ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ÷ “መንግስት የአረጋውያንን ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ” ገልጸዋል፡፡
በመንግስት በኩል እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር የአረጋውያንን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም እንዲሳተፍና የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና ሌሎች የበጎ አድራጎት ተቋማት ተወካዮች ለአረጋውያን ያላቸውን ክብር ለመግለጽ እግር የማጠብ ስነስርዓት አስጀምረዋል፡፡
ሚኒስትሯ÷ብሔራዊ ሁለገብ የአረጋውያን ማዕከል ግንባታ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ6 ሺህ 418 ካሬ ሜትር ላይ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በበዓሉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን÷ በመድረኩ የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት እውቅናና የምስጋና ሰርተፍኬት መበርከቱን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡