ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በኢትዮጵያ የሚተገበር የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በኢትዮጵያ የሚተገበር የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።
በኢትዮጵያ የግሎባል ኢነርጂ አልያንስ ለሰዎችና ፕላኔት፥ የመጀመሪያ የሆነውን ይህን ተደራሽ ታዳሽ ሀይል ለግብርና ስራዎች ፕሮጀክት አስጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብተሙ ኢተፋ፥ የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ብሎም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በጤና፣ በትምህርት፣ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ከተሞችን የሀይል ተጠቃሚ በማድረግ እና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የሚኖረውን ፋይዳ አንስተዋል።
በሀገሪቱ ከግማሽ በላይ ዜጎች የሀይል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ፥ ይህን ችግር ለመቅረፍ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተቀርጾ መተግበሩንና በ2030 የኤሌክትሪክ ሀይል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ተደራሽ ታዳሽ ሀይል ለግብርና ስራዎች ፕሮጀክት በፓይለት ደረጃ በኦሮሚያ ክልል በአራት ቦታዎች፣ በአማራ ክልል ሶስት ቦታዎች፣ በሲዳማ እና ደቡብ ክልሎች በአንድ ቦታ የሚተገበር ይሆናል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የመብራት፣ የንፁህ ውሃ እና የመንገድ ላይ መብራቶችን ያቀርባል።
እንዲሁም፥ 1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት መስኖ የሚያለሙ በናፍጣ የሚሰሩ ፓምፖችን በኤሌክትሪክ ፓምፕች መቀየር ያስችላል።
የፓይለት ፕሮጀክቱ ድርጅቱ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ባገኘው 20 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጀመር መሆኑን ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አመልክቷል።