የአቃቂ ቃሊቲ የቤት ልማት ግንባታዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ በኃላፊነት መስራት ይገባል- አቶ ጃንጥራር አባይ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአቃቂ ቃሊቲ የቤት ልማት ግንባታዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ በሙሉ ኃላፊነት እንዲሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ አሳስበዋል፡፡
አቶ ጃንጥራር የአቃቂ ቅሊቲ ተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ የጎበኙ ሲሆን፥ በዚሁ ወቅት በትንንሽ ምክንያቶች ግንባታው እንዳይጓተት የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ያስሚን ወሀብረቢ በበኩላቸው፥ ከፊል የግንባታ ስራ ቦታው ነፃ አለመሆን፣ የግብዓት እጥረትና ያለፈው የክረምት ወቅት ግንባታውን በተፈለገው ፍጥነት እንዳይከናወን ማድጋቸውን ገልፀዋል።
ኘሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዳይፈፀም በተለዩ ችግሮች ላይ በጉብኝቱ በተገኙ ከፍተኛ አመራሮች የመፍትሄ አቅጣጫ መቀመጡን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው፥ በበጀት ዓመቱ የሎት አንድን ግንባታ 70 በመቶ ለማድረስ፤ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉትን 20 ባለ አራት ወለል ብሎኮችን እስከ ጥር 30 ቀን 2015ዓ.ም ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡