Fana: At a Speed of Life!

አቶ አህመድ ሺዴ ከዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ከዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ እና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ከዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ እና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ጋር ተገናኝተው ነው የመከሩት።

ውይይቱ በኢትዮጵያ ፕሮግራም ላይ በተለይም በመንግስት ቅድሚያ በተሰጣቸው ጉዳዮች እንዲሁም የዓለም ባንክ በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚያደርጋቸው ድጋፎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት ለገጠሟት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ባንኩ ምላሽ በመስጠት ላሳየው ቁርጠኝነትና ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የአምራች ዘርፉን ሙሉ አቅም መጠቀም አስፈላጊነትን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ይህም ለሁሉ አቀፍ የስራ እድል ፈጠራ እና ዘላቂ እድገት፣ ማህበራዊ ትስስርን እና የግጭት ተጋላጭነት መቋቋምን ለመደገፍ እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን አንገብጋቢ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለመፍታት እና የማክሮ-ፊስካል መረጋጋትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ ከምትሠራቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም ኢትዮጵያውያን በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ያጋጠማቸውን የኢኮኖሚ ጫና ለማቃለል በማሰብ የተተገበረ መሆኑንም አስረድተዋል።

የተፈጥሮ አደጋዎችን መዋጋት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ አካሄዶች እንደሚያስፈልጉ በመጥቀስም፥ ድህነት፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አለመቻል፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች መዋጋት የተቀናጀ እርምጃ የሚሹ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑም ነው ያነሱት፡፡

የሰው ሃብትን በአግባቡ መጠቀም ፣ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ላይ ማተኮር፣ የጤና ዘርፉን ማሻሻልና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማሟላት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የዓለም ባንክ የምሥራቃዊ እና የደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን በርካታ ተግዳሮቶች ለመቋቋም ያደረገችውን ጥረት አድንቀዋል።

ለእነዚህ ለረጅም ጊዜ ለቆዩ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመስጠት ጠንካራ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረግን ይጠይቃል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.