የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የተጋላጭነት አውደ ጥናት እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ለሶስት ቀናት የሚያካሂደው የተጋላጭነት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
አውደ ጥናቱ በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላትና አደረጃጀቶች ፣ የታክስ ወንጀሎች እንዲሁም የቨርቹዋል ገንዘቦችና ቨርቹዋል ሃብቶች በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀሎች ያላቸውን ስጋትና ተጋላጭነት ለማጥናት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሌን ጊዜወርቅ÷ አውደ ጥናቱ በህግ የሰውነት መብት በተሰጣቸው አካላት፣ በታክስ ወንጀሎች እና ቨርቹዋል ገንዘቦችና ሃብቶች ስጋትና ተጋላጭነት በሚመለከት የሚካሄደው ጥናት መሠረት የተሟላ እውቀት ላይ በመመስረት ወንጀሎቹን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍና የአሠራር ስርዓት ለመዘርጋትና ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
ተቋማቸው ስራው የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።