የተመድ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ሴክሬታሪያት የኢትዮጵያን የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ዝግጅት አደነቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ሴክሬታሪያት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች እና ከኢትዮጵያ የበይነ መረብ አስተዳደር አዘጋጅ ኮሚቴዎች ጋር ተወያይቷል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ በህዳር ወር የምታስተናግድ ሲሆን÷ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የተለያዩ ኮሚቴዎች ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ልዑኩ ከብሄራዊ ኮሚቴ፣ ከአብይ ኮሚቴ እና በስራቸው ካሉ የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ጋርም ምክክር አድርጓል።
የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የዝግጅቱ አካል የሆኑና እስከ አሁን የተሰሩ ስራዎችም ለልዑኩ የቀረቡ ሲሆን÷ ልዑኩ የኢትዮጵያን ዝግጅት ማድነቁን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ልዑካኑ በቀጣይ ከኢትዮጵያ የፓርላማ አባላት እና ከዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር አማካሪ ኮሚቴ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡