Fana: At a Speed of Life!

የእናቶች፣ የህጻናት እና የወጣቶች ጤና ላይ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የእናቶች፣ የህጻናት እና የወጣቶች ጤና ዛሬም ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ ሁሉም አካላት በቅንጅት ሊሰሩበት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

የእናቶች እና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ከክልሎች ጤና ቢሮዎች፣ ከአጋር አካላትና ከሲቪል ተቋማት ጋር እያካሄደ ይገኛል፡፡

በዚሁ መድረክ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ÷ እስከ ጤና ኬላ ድረስ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ተግባራት በእናቶች፣ በጨቅላ ህጻናት እና ህጻናት፣ በወጣቶች ጤና ዙሪያ አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ክትባት ያሉ ግብአቶችን እና የጨቅላ ህጻናት ህክምና መሳሪያዎችን ከማሰባሰብ ጀምሮ ለማዳረስ የተደረገው ጥረትም የሚያኮራ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እና በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው አፈጻጸም ወጥ ባለመሆኑ ዝቅተኛ አፈጻጸም በታየባቸው አካባቢዎች ሁሉም አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የእናቶች ሞትን በመቀነስ ረገድ፣ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት፣ በስርአተ ምግብ ዙሪያ ፣ በእናቶች ሞት ቅኝትና ምዝገባ ስራና በመሰል አገልግሎቶች ላይም በ2030 ለማሳካት ከተያዘው ግብ አንጻር ብዙ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በመድረኩ በበጀት አመቱ ለነበሩ አፈጻጸሞች የማይተካ አበርክቶ ለነበራቸው አካላት የእውቅና ሽልማት መበርከቱን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.