የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ዲፕሎማሲ የወጣቶች ልዑክ ካርቱም ገባ

By Alemayehu Geremew

October 13, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ወንድማማችነትን እና የአረንጓዴ ልማት ዲፕሎማሲን ዓላማ ለማስተዋወቅ የኢትዮጵያ የወጣቶች ልዑክ ካርቱም ገባ፡፡

ወደ ካርቱም ያመራው የኢትዮጵያ ወጣቶች ልኡካን ቡድን በዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሳ አህመድ ተመርቷል፡፡

ልኡካን ቡድኑ በሚኖረው የሱዳን ቆይታ የአረንጓዴ ልማትንና አፍሪካዊ ወንድማማችነትን የማጠናከር ተልዕኮውን ይወጣልም መባሉን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይ ከሱዳን ወጣቶች ጋር በጋራ የችግኝ መትከል መርሐ-ግብር እና የሁለቱን ሀገራት ትስስር የሚያጠናክር ውይይት እንዲሁም ልምድ ልዉዉጥ ያካሂዳል ተብሏል።

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ እና የሱዳን መንግስት ባለሥልጣናት በካርቱም ዓለም አቀፍ አየር መንገድ በመገኘት ልኡካን ቡድኑን ተቀብለዋል፡፡