በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች መዋዕለነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ279 ሄክታር መሬት ላይ ለፋርማሲዩቲካል አምራቾች በተዘጋጀው ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶችና የዘርፉ አምራች ኩባንያዎች መዋዕለነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀርቧል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ አምራቾችን፣ ባለሀብቶችን እና አስመጪዎችን ዛሬ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን አስጎብኝቷል።
በጉብኝቱ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ረጋሳ÷ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለአምራች ኩባንያዎች አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን አሟልቶ አምራቾችን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዚህም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለመግባት ፍላጎት ያላቸው የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ አምራች ኩባንያዎች መዋዕለነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ አሁን ላይ ከ17 በላይ አምራች ኩባንያዎች በውስጡ እንደሚገኙ መገለጹን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡