Fana: At a Speed of Life!

አቶ አሕመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል ለምታደርገው ጥረት አጋሮች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል ለምታደርገው ጥረት የልማት አጋሮች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ እና የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ከቡድን ሰባት ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ጋር መክረዋል፡፡
በመድረኩ አቶ አህመድ ሺዴ እና ልዑካቸው ከተመረጡ የልማት አጋር አካላት፣ ለጋሾች ፣ አበዳሪዎች እና የአፍሪካ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው በሚቀጥሉባቸው ጉዳዮች እና በብድር አከፋፈል ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን በርካታ ችግሮች በመቋቋም በብሄራዊ ማሻሻያ አጀንዳ የሚታዩ ለውጦች ማስመዝገቧን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ በሂደት ለውጭ ድርጅቶች ክፍት ከማድረግ ባለፈ የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የልማት አጋር አካላትም ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ሂደት ግቡን እንዲመታና የሚያጋጥሟትን ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የሚደረግ ማንኛውም ድጋፍ በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመፍታት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚያበረከት መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ሚኒስትሩ የልማት አጋር አካላት ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የጀመረችውን አዲስ የለውጥ ሂደት እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን በአሜሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.