Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ውህደት እውን እንዲሆን እየሰራች ነው – አቶ አሸብር ባልቻ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅሙንና ተደራሽነቱን ለማሳደግ እና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ውህደት እውን እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ ተናገሩ፡፡

ከምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት አባል ሀገራት የተውጣጡ ከፍተኛ የኢነርጂ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የተሳተፉበትን መድረክ ሲከፍቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ የኃይል ተደራሽነት ሽፋኗን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራች ነው፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያና የማስተላለፊያ መስመሮችን በማስፋፋት በ2025 የኤሌክትሪክ ሽፋኑን መቶ በመቶ ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚውከሱዳን እና ከጂቡቲ የኃይል ትስስር መፈጠሩን ጠቅሰው በቅርቡ ከኬንያ ጋር የኃይል ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም ከተቀሩት የቀጣናው ሀገራት ጋር የኃይል ትስስሩን ለማስፋት የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት ለምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት ዓላማ መሳካት በቁርጠኝነት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት ዋና ፀሐፊ ኢንጂነር ሌቢ ቻንጉላ በበኩላቸው÷ ቀጠናዊ የኃይል ትስስሩ ከተመሰረተ የቆየ ቢሆንም አባል ሀገራቱ በኃይል ማመንጨት፣ በማከፋፈያ ጣቢያዎች እና በማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታ በሚፈለገው ደረጃ አለመጓዛቸው ትግበራውን በሚፈለገው መጠን እንዳላፋጠነው ጠቁመዋል።

ይሁንና ኢትዮጵያ ከጂቡቲ እና ከሱዳን ጋር የጀመረችው እና በቅርቡም ከኬንያ ጋር የምታደርገው የኃይል ትስስር በቀጣናዊ የኃይል ትስስር የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉ አበረታች ስራዎች ማሳያ ናቸው ብለዋል ፡፡

በዚህም የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት ቀጣናዊ ትስስር ሀገራቱን በማማከር እና አቅጣጫ በመስጠት ሚና እንዳለው መጠቆማቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.