Fana: At a Speed of Life!

የታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚ በወቅታዊ ሁኔታ እጅጉን እየተፈተነ ነው – አይ ኤም ኤፍ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ታዳጊ ሀገራት እና አዳዲስ ገበያዎች በዶላር ዋጋ መወደድ፣ በከፍተኛ የብድር ወለድ ጫና እና በንግድ ሰበብ ከሀገራቱ ወደ ውጪ በሚንቀሳቀስ ሐብት ኢኮኖሚያቸው እጅጉን እየተፈተነ መሆኑን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አስታወቀ፡፡

በተለይም ከፍተኛ የብድር ጫና ያለባቸው ሀገራት የፈተናው ዋና ገፈት ቀማሽ እንደሆኑ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ታዳጊ ሀገራት በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውጥረት እና ሥጋት ውስጥ እንደገቡም ነው “አይ ኤም ኤፍ” ያመላከተው፡፡

ዳይሬክተሯ የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ባካሄዱት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ÷ “በዚህ ፈታኝ ወቅት እያቆጠቆጡ ያሉ ገበያዎችንና ታዳጊ ሀገራትን መደገፍ አለብን” ሲሉም በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ ከአንጻራዊ መረጋጋት እና ተገማች ኢኮኖሚያዊ ትንበያ ወጥቶ ወደ ተለዋዋጭ ፣ ያልተረጋጋ እና ኢ-ተገማች መሠረታዊ ሽግግር ውስጥ መግባቱንም በስብሰባው አንስተዋል፡፡

ፖሊሲ አውጪዎች የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ ፣ የተጤነ ፊስካል ፖሊሲ እውን ለማድረግ እንዲሁም የተረጋጋ ፋይናንስ እንዲኖር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

የኮቪድ19 ወረርሽኝ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለ93 ሀገራት የ260 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ተቋሙ ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ወዲህም ለ18 አዳዲስ መርሐ-ግብሮች ወደ 90 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የሺንዋ ዘገባ ያመላክታል።

ተጨማሪ 28 ሀገራትም የተቋሙ ፈንድ ተጠቃሚ ለመሆን መጠየቃቸውን ነው ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም ያስታወቀው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.