Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና የሱዳን የመረጃ ተቋማት ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያና የሱዳን የመረጃ ተቋማት ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የሱዳን ሪፐብሊክ አቻው ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ  የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር የሚያከናውኗቸውን ሥራዎችና ስምሪቶች  አጠናክረው ለመቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውንና ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት  በላከው መግለጫ እንዳመለከተው÷ በሱዳን  ሪፐብሊክ ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ  ዳይሬክተር ጀነራል ተቀዳሚ ሌተናል ጀነራል አሕመድ ኢብራሂም  ሙፋደል የተመራ የልዑክ ቡድን ዛሬ በተቋሙ ጉብኝት አድርጓል፡፡

ከጉብኝቱ በኋለ በነበረው መድረክም የሁለቱ ሀገራት እንዲሁም የቀጣናውን ወቅታዊ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች የሚመለከቱ አጀንዳዎች ተነስተው ምክክር ተደርጓል፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመድረኩ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያና ሱዳን ተመሳሳይ ባህል፣ቋንቋ፣ ሃይማኖት እንዲሁም ሰፊ ድንበር የሚጋሩ በመሆናቸው የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ አድርጎታል፡፡

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኘውን ትሩፋት በጋራ በመቋደስም ትስስሩን ለማጠናከር  ይሠራል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት  ከሱዳን ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ  ጋር መረጃ በመለዋወጥና በአቅም ግንባታ መስኮች የሚያደርገውን ትብብር  በማጠናከር ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች  እንዲሁም ሕገወጥ የገንዘብ፣ የመሣሪና የሰዎች ዝውውር የሚያስከትሉትን ተፅዕኖዎች ለመቀነስ በትብብር እንደንሚሠራ  አቶ ተመስገን  ገልጸዋል፡፡

በተለይ በቀጣናው ከፍተኛ ሥጋት የሆነውን ሽብርተኝነት ለመከላከል የሚካሄዱ የመረጃ ልውውጦችንና የጋራ ስምሪቶችን በማጠናከር በደም የተሳሰሩትን  የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ደኅንነት ለማረጋገጥና ተጠቃሚነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ  የትብብር አድማሶችን ለማስፋት ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሱዳን ወሳኝ ስትራቴጂክ አጋር ሀገር ሆና እንደምትቀጥል መንግሥት በጽኑ እንደሚያምን ያነሱት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር  ጀነራል አቶ ተመስገን በሁለቱ ሀገራት ብሎም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በመረጃና በጸጥታ ተቋማቶቻቸው መካከል የሚደረገውን ትብብር እና አጋርነት በማጠናከርም የጋራ የደኅንነት ሥጋቶችን ለማስወገድ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

የሱዳን ሪፐብሊክ ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ተቀዳሚ ሌተናል ጀነራል አሕመድ ኢብራሂም ሙፋደል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የመረጃና ደኅንነት ተቋም ያደረጉት ጉብኝት በሪፎርሙ ሂደት ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን በርካታ የሚጋሯቸው ጉዳዮች በመኖራቸው የሁለቱ ሀገራት የመረጃ ተቋማት የጋራ የደኅንነት ሥጋቶችን ለማስወገድ በትብብር መሥራታቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመው በተለይ ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊም ሥጋት የሆነው ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚደረጉ የአጋርነት ሥራዎች  እና ኦፕሬሽኖች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡

የመረጃ ልውውጥም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን የሚዋሰኑበት ድንበር ረጅም በመሆኑ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ጨምሮ የተለያዩ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን መከላከል እንደሚገባ በምክክሩ  መነሳቱንም  ተቀዳሚ ሌተናል ጀነራል አሕመድ ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡

የወሰን አካባቢዎችን ሰላም በማረጋገጥ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚነት ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር የሚገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የሱዳን ሪፐብሊክ አቻው ጀነራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ  በቀጣይም ቋሚ የጋራ  መድረኮችን በማዘጋጀት ትብብራቸውንና አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.