Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የምዕራባውያን አተያይ የተዛባ ነው – ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራልድ

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ለተከሰተው ግጭት መራዘም የምዕራባውያን አተያይና ምላሽ ሚዛናዊ አለመሆን የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከቱን ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራልድ ገለጹ፡፡

በካናዳ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራልድ በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በተካሄደው የኅብረተሰብ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራልድ ፥ በኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ባለው ጦርነት ምዕራባውያኑ ሚዛናዊ ያልሆነ እና አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት እንደ ነበራቸው ገልጸዋል፡፡

ምዕራባውያኑ የሰሜኑን አካባቢ የመከፋፈል አዝማሚያም እንደነበራቸው እና በጦርነቱ ወቅት በአፋርና አማራ ክልሎች ለነበሩ ተጎጂዎች ሰብዓዊ ዕርዳት ለማድረስ እምብዛም ትኩረት እንዳልሰጡት አብራርተዋል፡፡

ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራልድ ÷ ከሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል ጦርነት በኋላ በሂደት ዘላቂ ሰላም መገንባት አለበት ብለዋል፡፡

ለሰላም፣ ለደኅንነት፣ ለተሻለ የዜጎች አኗኗርና ለመልሶ ግንባታ በትኩረት መሰራት ይኖርበታልም ነው ያሉት።

ፕሮፌሰሯ የኢትዮጵያ ህዝብ እና ዳያስፖራው ማኅበረ-ሰብ በሃሳብ ሳይከፋፈል አንድ ሆኖ በመቆሙም የምዕራባውያኑን ጫና መቋቋም እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡

የጠነሰሱትን የመከፋፈልና ኢትዮጵያን የብጥብጥ ማዕከል የማድረግ ዓላማ መጨናገፍ እንደተቻለም ነው ያነሱት፡፡

መላው የትግራይ ህዝብ የአሸባሪው ህውሓት ደጋፊ እንዳልሆነና በጦርነቱም ተጎጂ መሆኑን በጥናት አስደግፈውም እውነታውን አቅርበዋል።

የትግራይ ህዝብ ሰላምና አንድነት እንዲሁም የፖሊቲካ ለውጥና ሰብዓዊ ዕርዳት በአግባቡ እንዲደርሰው የሚፈልግ ብሎም ለሀገራዊ አንድነት ቁርጠኛ ፍላጎት ያለው መሆኑን በህዝባዊ መድረኩ ላይ ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፥ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራልድ ከ2002 ጀምሮ በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል፣ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን ሰርተዋል፣ ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ባለችበት ሁኔታ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አስረድተዋል።

ጅማ ዩኒቨርስቲ ካናዳዊቷ ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራላንድ ለኢትዮጵያ ላበረከቱት መልካም ተግባር እውቅና ሰጥቷል፡፡

ፕሮፌሰር አን ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በገባችበትና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ተቋማት በዘመቱባት ወቅት ፥ በተለያዩ መንገዶች የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ለማሳየት ባደረጉት ጥረት ነው እውቅናው የተሰጣቸው።

በተመስገን አለባቸው እና ሙክታር ጣሃ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.