Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ 13 የቤቲንግ ስራ ድርጅቶችና የ109 አንቀሳቀሾቻቸውን የባንክ ሒሳብ አገደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በፋይናንስና ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎችን በሚፈጽሙ አካላት ላይ መውሰድ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖረው በጥቁር ገበያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የምንዛሪ መዛባት እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል የወንጀሉ ተዋንያንን እንቅስቃሴ በመከታተል የባንክ እንቅስቃሴያቸውን ማገድ አንዱ ነው፡፡

አግባብነት ካላቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወንም ሌላኛው እርምጃ ነው፡፡

በአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ክትትል ሲካሄድባቸው ከቆዩ የወንጀሉ ተዋንያን ውስጥ ቤቲንግ በሚል ስያሜ የሚታወቁ የውርርድ ድርጊቶችን የሚያከናውኑ አካላት መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ድርጅቶቹ ከህብረተሰቡ የሚሰበስቡትን ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በመጠቀም በጥቁር ገበያ የውጭ ሀገር ምንዛሬ ግዢ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን በተደረገ ክትትል ማረጋገጥ መቻሉም ነው የተገለጸው፡፡

ስለሆነም የታክስ ማጭበርበርን ጨምሮ በህገ-ወጥ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ግዢ ወንጀል ድርጊት ተሳታፊ መሆናቸው የተደረሰባቸው 13 የቤቲንግ ስራ ድርጅቶችና 109 አንቀሳቀሾቻቸው የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ በማድረግ በቀጣይ ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ የማድረግ ውሳኔ መተላለፉ ተገልጿል፡፡

በእነዚህና በሌሎችም ዘርፎች በሚንቀሳቀሱና መሰል የወንጀል ተግባር ላይ በሚሳተፉ አካላት ላይ ቀጣይነት ያለው ክትትልና ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

በወንጀል ተግባሩ ተሳታፊ እየሆኑ ያሉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አገልግሎቱ በድጋሚ አሳስቧል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.