Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና የአፋር ህዝቦች የሰላም መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና የአፋር ወንድም ህዝቦች በከሚሴ ከተማ የጋራ የሰላም የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

የጋራ የሰላም ምክክር መድረኩ የተጀመረው በኃይማኖት አባቶች ምርቃን ነው፡፡

የሁለቱ ህዝቦች የኖረ የጋራ እሴት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት መንገድ በተለያዩ የኃይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች እና አባ ገዳዎች የዱዓና የፀሎት ስነስርዓት ተካሂዷል።

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በጋራ የሰላም ምክክር መድረኩ እንደገለጹት÷ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የኖረ የጋራ እሴት አለ፡፡

ይህንን የበለጠ በማጠናከር ለጋራ እድገታችን ልንጠቀምበት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መፈቃቀድ ማሳያው ብዙ ነው ያሉት አቶ አህመድ አሊ÷ መልካም ግንኙነታችን እንዳለ ሆኖ ሰላም እንዳይኖር ችግር የሚፈጥረው የጋራ የኢትዮጵያ ጠላት ሸኔን እና የጥፋት ተልዕኮውን ማክሸፍ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።

የአፋር ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሀጂ ብላይ አህመድ በበኩላቸው÷ የአፋር ህዝብ እና በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በጠላት ወረራ ወቅት የነበራቸው ትብብር እና ጠላትን ለማጥፋት በተደረገው ጥረት ያሳዩት የጋራ ተጋድሎ የሚደነቅ መሆኑን አስታውሰዋል።

አሁንም በተለያዩ ጉዳዮች ግንኙነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው÷ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና የአፋር ወንድም ህዝቦች በድንበር ተዋሳኝ ብቻም ሳይሆኑ በደም የተሳሰረ የጋራ ስነ ልቦና ያላቸው ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

የጋራ ጠላቶች በሁለቱ ህዝቦች መካከል  ግጭት እንዳለ ለማስመሰል ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም ነው የተባለው።

በጋራ የሰላም ምክክር መድረኩ ከአፋር ክልል ሰባት ወረዳዎች የተውጣጡ የጎሳ መሪዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና አባ ገዳዎች ተገኝተዋል።

በሁለቱ ተዋሳኝ ህዝቦች መካከል ለግጭት ምክንያት የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች በጥናት ቀርበው ውይይት እየተደረገ ነው።

በእሸቱ ወልደሚካኤል

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.