ጠንካራ አፍሪካን መገንባት ማለት ሀገር በቀል አፍሪካ መር መፍትሄዎችን ማዘጋጀት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠንካራ አፍሪካን መገንባት ማለት ድንገተኛ ክስተቶችን መቋቋም ብቻ ሳይሆን በትኩረት ማቀድ እና ሀገር በቀል አፍሪካ መር መፍትሄዎችን ማዘጋጀት መሆኑን አስታወቁ።
በአፍሪካ የሰላም፣ ጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክረው የጣና ፎረም በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፥ ፎረሙ በአፍሪካ ለሰላምና ደህንነት ስጋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።
አያይዘውም “አፍሪካን መገንባት ማለት የድንገቴ ክስተቶችን መቋቋም ብቻ ሳይሆን በትኩረት ማቀድ እና ሀገር በቀል አፍሪካ መር መፍትሄዎችን ማዘጋጀት ነው” ብለዋል።
አፍሪካ ለዓየር ንብረት መበከል አበርክቶዋ አነስተኛ ቢሆንም ለዓየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ መሆኗን ጠቅሰው፥ በዚህ ረገድ ከሶስት አፍሪካውያን አንዱ ለውሃ ችግር ተጋላጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የፀሃይና ንፋስ ሃይልን ጨምሮ በታዳሽ ሃይል የምታደርገውን ልማት እንደምትቀጥልም ነው የገለጹት።
አያይዘውም ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረቷን ለመቅረፍ ብቻ ሳይሆን ያላትን ሃይል በአግባቡ በመጠቀም ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ለመላክ እየሰራች መሆኗንም አንስተዋል።