Fana: At a Speed of Life!

ፑቲን ኔቶ ከሩሲያ ጋር ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ከገባ “ዓለም አቀፍ ጥፋት” ያስከትላል ሲሉ አስጠነቀቁ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከሩሲያ ጋር ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ከገባ “ዓለም አቀፍ ጥፋት” ያስከትላል ሲሉ አስጠነቀቁ።

ፕሬዚዳንቱ በአስታና እየተካሄደ ባለው የማዕከላዊ እስያ – ሩሲያ ስብሰባ ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ዩክሬን ተሸናፊ ከሆነች ኔቶ ጦሩን ሊልክ ይችላል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፥ “ይህ አደገኛ እና ወደ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ሊመራ የሚችል አካሄድ ነው” ሲሉ መልሰዋል።

“ከዚህ ጋር በተያያዘ ይሆናል በሚል አስተያየት የሚሰጡ አካላትም እንዲህ አይነቱ አደገኛ ጥፋት እንዳይከሰት መከላከል የሚችሉበት በቂ እውቀት ይኖራቸዋል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል ፑቲን በምላሻቸው።

አያይዘውም ከዩክሬን ቀውስ ጋር በተያያዘ “ሽንፈት” የሚለውን ቃል ምንነት መረዳት አስፈላጊ መሆኑንን አንስተዋል።

“ሽንፈትን ሁሉም በተለየ መንገድ ሊረዳው ይችላል” ያሉት ፑቲን “ክሬሚያ በፈረንጆቹ 2014 የሩሲያ አካል ለመሆን ድምጽ መስጠቷን አንዳንዶች እንደሽንፈት ሊመለከቱት ይችላሉ” ሲሉም አስረድተዋል።

ምዕራባውያን የሩሲያ ዩክሬን ግጭት ከጀመረበት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በርካታ ቢሊየን ዶላሮችን ፈሰስ በማድረግ ለዩክሬን የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጋቸው ይነገራል።

አሜሪካ በተደጋጋሚ ለዩክሬን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ስታቀርብ መቆየቷን ምንጮችን ዋቢ ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ያመላክታሉ።

የኔቶ አባል ሀገራትም ባለፈው ሩሲያ በዩክሬን መዲና ኪዬቭ የሚሳኤል ጥቃት ከፈጸመች በኋላ፥ ለዩክሬን ዘመናዊ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያዎችን ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጋቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የኔቶ ዋና ፀሃፊ ዬንስ ስቶለተንበርግ የቃል ኪዳን ድርጅቱ በሩሲያ ዩክሬን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ አይደለም ቢሉም፥ ከሰሞኑ ግን “የዩክሬን መሸነፍ ለምዕራባውያን ሽንፈት” ነው ሲሉ አምነዋል።

“ይህን መሰሉን ኪሳራ ለማስወገድም ኔቶ ለዩክሬን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ጀምሯል” ነው ያሉት።

የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭም የዋና ፀሃፊው ንግግር ኔቶ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጣልቃ መግባቱን አመላካችና ማረጋጋጫ ነው ማለታቸውን አር ቲ በዘገባው አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.