የማጃንግ የተፈጥሮ ደን እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ተቋም የተመዘገበው የማጃንግ የተፈጥሮ ደን እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ፡፡
በማጃንግ ባዮስፌር ሪዘርቭ ጥበቃ ዙሪያ በሜጢ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ በማጃንግ ዞን በሚገኘው የተፈጥሮ ደን ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም የአካባቢው ማህበረሰብ ለደን ጥበቃው ልዩ ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል፡፡
ደኑ በሕገ ወጦች ጉዳት እየደረሰበት በመሆኑ ከጥፋት ለመታደግ የሁሉም የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል መባሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
225 ሺህ ሔክታር የሚጠጋ የቆዳ ስፋት ያለው የማጃንግ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን÷ በውስጡ 550 የሚደርሱ የእጽዋት፣ ከ180 በላይ የአዕዋፍ፣ 33 የአጥቢ እንስሳትና 20 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡