Fana: At a Speed of Life!

በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የውኃ ተቋማትን ወደ ሥራ ለማስገባት የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የሚገመቱ የውኃ ተቋማትን በአስቸኳይ ጥገና መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የተደረገው ጥረት ውጤት ማስመዝገቡ ተገለጸ፡፡

የክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ የ2015 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድን እየገመገመ ነው፡፡

የቢሮው ኃላፊ ማማሩ አያሌው የሽብር ቡድኑ በ86 ወረዳዎች በሚገኙ የውኃ ተቋማት ላይ ባደረሰው ጉዳት ስምንት ሚሊየን ሕዝብ የንፁህ ውኃ አቅርቦት ተቋርጦበት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የውኃ ተቋማቱን መልሶ በመገንባት 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም 300 አነስተኛ ተቋማትና ከ64 በላይ ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን መልሶ ወደሥራ ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የንፁህ መጠጥ ተደራሽነትን፣ የአማራጭ ኢነርጂ አቅርቦትን፣ የከተማ ሳኒቴሽን፣ የውኃ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ሥራዎችን በውጤታማነት ለማከናወን እየተሠራ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የውኃ አቅርቦትን በ3 ነጥብ 4 በመቶ ለመጨመር መታቀዱም በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡

1ሺህ 682 ከባድ ጥገናዎች እንደሚደረጉ እና በከተሞች ያለውን 22 ነጥብ 62 በመቶ የውኃ ብክነት ወደ 20 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መታቀዱም ተመላክቷል፡፡

የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ እና በአጋርነት ለደገፉ አካላት እውቅናና ምስጋና እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡

በሙሉጌታ ደሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.