የሀገር ውስጥ ዜና

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ባሻገር በማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች የበለጠ መሥራት አለበት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

By Tamrat Bishaw

October 15, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ሥራው ባሻገር በማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች የበለጠ መሥራት አለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም÷ ዩኒቨርሲቲው ከአካዳሚክ ሥራው ጎን ለጎን ግቢዎቹን በአትክልትና ፍራፍሬ ለማስዋብ ያደረገውን ጥረት ተመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የጀመረው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው÷ በሚያከናውነው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ ከራሱ አልፎ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ባሻገር በማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች የበለጠ መሥራት እንዳለበት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡