ዳያስፖራውን ያሳተፈ የጎዳና ላይ ሩጫ በአሌክሳንድሪያ ከተማ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዳያስፖራውን ማህበረሰብ ያሳተፈ የ 5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በቨርጂኒያ ግዛት አሌክሳንደሪያ ከተማ ተካሂዷል፡፡
“አብሮነት መሻል ነው” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ውድድር በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት ፋጡማ ሮባ፣ አትሌት ሚሊዮን ወልዴ፣ አትሌት ታሪኩ በቀለና አትሌት ቁጥሬ ዱለቻ ተሳትፈዋል፡፡
የዘንድሮው ግራንድ አፍሪካን ራን ለአራተኛ ጊዜ እንደተከናወነ የተገለጸ ሲሆን÷ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ውድድሮች ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት መዋላቸው ተገልጿል።
በዘንድሮው የውድድር ፕሮግራምም በአርቲስት ሰለሞን ቦጋለ የሚመራው ሕብረት ለበጎ አድራጎት ድርጅት ለሚያሰራው የኩላሊት ሕክምና ሆስፒታል ገቢ ተሰብስቧል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተካፈሉበት ውድድር በአዋቂዎች የ5 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በሕጻናት የአንድ ኪሎ ሜትር ሩጫ መካሄዱን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡