Fana: At a Speed of Life!

ቻይና አዳዲስ የልማት ተሞክሮዎችን በመቀመር የጀመረችውን እድገት አጠናክራ ትቀጥላለች – ሺ ጂንፒንግ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና አዳዲስ የልማት ንድፎችን እና ተሞክሮዎችን በመቀመር የጀመረችውን የልማት እድገት አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ገለጹ፡፡

20ኛው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በዋና ከተማዋ ቤጂንግ መካሄድ ጀምሯል፡፡

የፓርቲውን ሪፖርት ያቀረቡት ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ÷ ቻይና አዳዲስ የልማት ንድፎችን በመቀመር እና በመተግበር የጀመረችውን እድገት አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

በሁሉም ረገድ ዘመናዊ እና የበለጸገች ሾሳሊስት ሀገር ለመገንበት ከፍተኛ ጥራት ያለው የልማት መንገድ መከተል አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም የሶሻሊዝም ፍልስፍናን አሁን ካለው የቻይና ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተለይም የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን ማሳደግ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማበረታታት እና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስሮች ላይ አዎንታዊ መስተጋብር መፍጠር እንደሚገባ አውስተዋል፡፡

የቻይናን ኢኮኖሚ በማሳደግ የዜጎች ብልጽግና እውን ለማድረግም በሁሉም ዘርፍ በአንድንት እና በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸውን ሺንዋ ዘግቧል፡፡

ኮሚኒስት ፓርቲ በቻይና አዲስ የለውጥ ትሩፋት አምጥቷል ያሉት ሺ ጂንፒንግ፥ በዚህም በሀገሪቱ ድህነትን በማጥፋት የዜጎችን ህይወት ያሻሻሉ አመርቂ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.