የሀገር ውስጥ ዜና

በልደታ ክ/ከተማ የተገነቡ 10 የተማሪ መመገቢያ ማዕከላት ተመረ

By Melaku Gedif

October 16, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ የተገነቡ 10 የተማሪ መመገቢያ ማዕከላት በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እንዳሉት÷ የምገባ ማዕከሎች በከተማ አስተዳደሩና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍና ልዩ ክትትል የተገነቡ ናቸው፡፡

የምገባ ማዕከላቱ ጤናው የተጠበቀ አምራች ትውልድ የሚፈጥሩ፣ የተማሪዎችንና የወላጆችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የሚያቃልሉ እንዲሁም የትምህርት ጥራት የሚረጋገጥባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጃንጥራር ማዕከላቱ ለእናቶች የስራ እድል እንደፈጠሩ መናገራቸውንም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኙ 128 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተማሪ መመገቢያ ማዕከላት መገንባታቸውንም አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ ከተማ የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከዓለም ባንክ ባገኘው ድጋፍ ያስገነባቸውን 15 ሼዶች ለአምራቾች አስተላልፏል፡፡

በዓለም ባንክ ድጋፍ በ70 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡት ሼዶች ቀደም ሲል በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ለነበሩ እና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ስልጠና ወስደው ለተመረቁ 162 ተጠቃሚዎች መተላለፋቸው ነው የተገለጸው፡፡