Fana: At a Speed of Life!

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመንገሺ ወረዳ እየለማ የሚገኝ የስንዴ ማሳን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በማጃንግ ዞን መንገሺ ወረዳ በሙከራ ደረጃ እየለማ የሚገኝ የስንዴ ማሳን ጎብኝተዋል፡፡
 
በመርሐ ግብሩ የተሳተፉት ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ÷ የጋምቤላ ክልል በስንዴ ምርት ከሁሉም ክልሎች ወደ ኋላ መቅረቱን አንስተዋል።
 
በአሁኑ ሰዓት በተለያየ የክልሉ አካባቢዎች ስንዴን በስፋት ለማምረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ በሙከራ ደረጃ ያለው ተግባር ውጤት ካስገኘ በስፋት እንደሚከናወን አመልክተዋል።
 
የማጃንግ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ማይክል በበኩላቸው÷ የስንዴ ምርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቁመው÷ በዞኑም በ20 ሄክታር መሬት ላይ ሙከራ መደረጉን አስታውቀዋል።
 
የሙከራ ሂደቱ ውጤታማ መሆን ከቻለ ወደ ሌሎች ቀበሌዎች የማስፋቱ ስራ እንደሚከናወን የገለጹት አቶ አብርሃም÷ ሙከራው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አብራርተዋል።
 
የአካባቢው መሬት ለበርካታ አዝዕርት ምቹ መሆኑ እና የሙከራ ስንዴው በ90 ቀናት ሊደርስ የሚችል ዝርያ እንደሆነ መገለጹንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.