በገንዘብ ሚኒስትሩ የተመራው ልዑክ ከ“አይ ኤም ኤፍ” ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ የተመራው ልዑክ ከዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማካሄዱ ተገለጸ፡፡
ልዑካን ቡድኑ ከዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ጋር የመከረው በአሜሪካ እየተካሄደ ካለው የዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በውይይቱ ከቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ጣሊያን የሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች አማካሪዎች ጋር መምከራቸው ተገልጿል፡፡
ውይይቱ በዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም ወሳኝ የልማት አጋርነት ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል፡፡
በተለይም በችግር ወቅት ተቋሙ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረስ በሚችልበት አግባብ ላይ መምከራቸው ነው የተመለከተው፡፡
ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ተደራራቢ ጫናዎችም እንድትወጣ “አይ ኤም ኤፍ” የልማት አጋር መሆን በሚችልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸው ተገልጿል፡፡