ብልጽግና ፓርቲ 20ኛው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ብሔራዊ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ 20ኛው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ብሔራዊ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገለጸ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የ20ኛው የቻይና ኮሚስኒስት ፓርቲ ብሔራዊ ጉባዔን አስመልክቶ መልካም ምኞታቸውን ለቻይና ፕሬዚዳንት ሺዥ ፒንግ፣ ለመላው አመራር እንዲሁም ለፓርቲው ዋና ፀሀፊ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ፥ ባለፉት ዓመታት በሺ ጂንፒንግ መሪነት ጥራት ያለው እና ፈጠራ የታከለበት እድገት በማስመዝገብ በርካታ ሕዝብ ከድህነት ማውጣት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሸኤቲቭ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራትን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ፓርቲው በጉባዔው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ለቻይና ብቻ ሳትሆን ለመላው ዓለም ተጽዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሲፒሲ በ20ኛ ጉባዔውም ለዓለም ሰላም መረጋጋት እና ብልጽግና ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አመርቂ ውጤቶችን በተለያዩ ዘርፎች ማስመዝገቡንም ተናግረዋል፡፡
ወደ ፊትም የብልጽግና እና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲዎች ግንኙነትን በማጠናከር የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ፓርቲያቸው ቁርጠኛ መሆኑን አቶ አደም አረጋግጠዋል፡፡
ጉባኤው የተሳካ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውንም ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡