Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን የመከላከል ርምጃ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭት፤ ሕወሐት ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በሙሉ ዐቅሙ የከፈተውን ጥቃት ተከትሎ የመጣ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው። ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያዝያ ወር ያወጀውን በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተኩስ አቁም የጣሰ ነው። የመንግሥት ጥረት ምንም ዋጋ ስላልተሰጠው፣ ሕወሐት በሁለት ዓመት ውስጥ ሀገሪቱን ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ግጭት አስገብቷታል።

ሕወሐት ሦስተኛውን ግጭት የከፈተው በአፍሪካ ኅብረት በኩል በሚደረገው የሰላም ንግግር፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ላይ ለመነጋገር የኢትዮጵያ መንግሥት ዝግጅነቱን ከገለጠ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለልዩ መልእክተኞችና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ጥቃት ለመሠንዘር ሕወሐት ያለውን ዝግጁነት አመልክቶ ነበር። ሕወሐት ለተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት በበተነው ደብዳቤ ላይ ይሄንን ጥቃት የመክፈት ፍላጎቱን በግልጽ አመልክቷል። በመሆኑም አሁን ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ብቸኛ ተጠያቂው ሕወሐት መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ጊዜና ቦታ ከተሰጠውም ሌላ ዙር ግጭት እንደሚፈጥር ከሰሞኑ መግለጫዎቹ ለመረዳት ይቻላል።

ሕወሐት በሙሉ ዐቅሙ ጥቃት ከመክፈቱ በፊት የኢትዮጵያን የአየር ክልል ደጋፊዎቹ በሆኑ የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ሲያስደፍር ቆይቷል። በዚህም የተነሣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ አስገድዶታል። የኢትዮጵያመንግሥት የሚወስዳቸውርምጃዎች የግድ አስፈላጊ የሆኑት በሕወሐት ተደጋጋሚ ጥቃት የተነሣ ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋርተቀናጅቶ በሚፈጽማቸውተግባራት ምክንያት ጭምር ነው። ስለሆነም የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር የኢትዮጵያ መንግሥት የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የፌዴራል ተቋማትንና ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን የግድ መጠበቅ አለበት ማለት ነው። ይህም የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በተለይም የአየር ክልልን በሚገባ ከማስከበር አንጻር መጠበቅን የግድ አድርጎታል።

እነዚህ ተግባራት መፈጸሙ መንግሥት ሰብአዊ ርዳታን ለተረጂዎች በተገቢው ሁኔታ እንዲያሣልጥ የሚረዳው ይሆናል። በአንድ በኩል እነዚህን ዓላማዎች እያስፈጸመ በሌላ በኩል ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት ለሚካሄደውየሰላምውይይት ዝግጁመሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በድጋሚ ያረጋግጣል። ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁለንተናዊና በንግግር ላይ የተመሠረተ ስምምነት አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት ያምናል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አግባብነት ባላቸዉ አሠራሮችና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕጎች በጽኑ የሚገዛ መሆኑን መንግሥት ግልጽ ለማድረግ ይፈልጋል። ንጹሐን እንዳይጎዱ ለመከላከል እንዲቻል የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ጦርነቱ በከተሞች ውስጥ እንዳይደረግ ጥንቃቄ እያደረገ ይገኛል። ይሄንን በጽኑ ለመፈጸም እንዲቻልም ለሁሉም ተዋጊ አሐዶች ጥብቅ መመሪያ ተላልፏል።

ከዚህም ባሻገር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሆኑ አካባቢዎች ሰብአዊ ርዳታ በተሻለ መንገድ መቅረብ እንዲችልና የርዳታ ሠራተኞች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን መንግሥት ከርዳታ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነው። ሕወሐት ንጹሐንን እንደ ጦር መከላከያ የመጠቀምና ሲቪል ተቋማትን ለወታደራዊ ሠፈርነት የመጠቀም የቆየ ልማድ አለው። ስለሆነም ሕዝቡና የርዳታ ሠራተኞች ራሳቸውን ከሕወሐት ወታደራዊ ተቋማት እንዲያርቁ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ ያደርጋል። የርዳታ ሠራተኞችን ጨምሮ በሲቪሎችን ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት መንግሥት ኀዘኑን በዚህ አጋጣሚ ይገልጣል። እውነቱን ለማወቅና ያልተገደበ የርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል ጉዳቶች ከተከሠቱ የሚያጣራ ይሆናል።

በመጨረሻም፣ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎቹን ደኅንነት ለመጠበቅ በሕግ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን ለመወጣት የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ዝግጁነት በዚሁ አጋጣሚ ያረጋግጣል።

ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.