የኅዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማሰሪያ በመሆኑ ለፍጻሜ ለማብቃት በትብብር እንሠራለን – የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማሰሪያ በመሆኑ የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን ለፍጻሜ ለማብቃት በትብብር እንሰራለን ሲሉ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በመገኘትም የግንባታውን ሂደትና አሁናዊ ገጽታ መጎብኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገር አንድነት፣ ለሠላም መስፈንና ለልማት መረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነው ቃል የገቡት።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ለግድቡ ግንባታ ስኬት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦም አድንቀዋል፡፡
በመንግስት በኩል የታየው ቁርጠኝነትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን ዐሻራ ያረፈበትን ታላቁን የኢትዮጵያን ኅዳሴ ግድብ የመጎብኘት ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ባሻገር በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም የራሳቸውን ዐሻራ ለማሳረፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስም የኢትዮጵያ ህዝብ የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡