በአማራ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ አኩሪ አተርን ለማምረት ሰፊ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ በክላስተር የለማ የአኩሪ አተር ማሳን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሐፍ ÷ በአማራ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ በሚካሄደው ርብርብ አኩሪ አተርን ለማምረት ሰፊ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ38 ሺህ ሄክታር ላይ ያረፈውን የኩታ ገጠም ምርት መጎብኘታቸውንም አንስተዋል፡፡
በጠገዴ ወረዳ አዲስ ዓለምም በኩታ ገጠም 1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ የተመረተውን አኩሪ አተር መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
ያስገኙት ምርት በእጅጉ አበረታች መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ÷ ይህም በስንዴ አምራችነት የተገኘውን አስደሳች ውጤት በሌሎች ምርቶችም እንደሚቀጥል ያመላክታል ነው ያሉት።
ሀገራችን የምግብ ዋስትናዋን አረጋግጣ በዓለም ገበያ በምርቶቿ መሳተፏ የሩቅ ጊዜ ህልም ሳይሆን፣ እየቀረበ የሚገኝ የጥረት ውጤት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።