Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ እና ዩክሬን ከፍተኛ ያሉትን የእስረኛ ልውውጥ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ እና ዩክሬን ከፍተኛ ነው ያሉትን የእስረኛ ልውውጥ ማድረጋቸውን አስታወቁ፡፡

ሩሲያ 108 ሴት የዩክሬን ወታደሮችን ስትለቅ ዩክሬን ደግሞ በአብዛኛው ሲቪል የሆኑ 110 ሩሲያውያን በምትኩ መልቀቋን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከ108ቱ የዩክሬን ሴት ወታደሮች ውስጥ ሁለቱ ወደ ዩክሬን መመለስ አለመፈለጋቸውንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡

በእስረኛ ልውውጡ ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በዩክሬን ታስረው የነበሩ 72 የሩሲያ መርከበኞችም ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተዘግቧል፡፡

ከዩክሬን ተለቀው ለተመለሱ ሩሲያውያን ተገቢ የህክምና እና የስነ ልቦና ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ዩክሬን በበኩሏ የእስረኛ ልውውጡ በተለያዩ የሩሲያ ክፍሎች እና በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሆኑ የዩክሬን ግዛቶች ታስረው የነበሩ 30 ወታደሮችን እና መርከበኞችን ጭምር ያካተተ መሆኑን ገልጻለች፡፡

ሁለቱ ሀገራት ባለፈው ሐሙስም የ20 ወታደሮች ልውውጥ ማድረጋቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ሞስኮ እና ኪየቭ ጦርነቱ ከተጀመረ የካቲት ወር አንስቶ በተደጋጋሚ የእስረኛ ለውውጥ ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.