በአቶ ዑመር ሑሴን የተመራ ልዑክ በዓለም ምግብ ፎረም እየተሳተፈ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን የተመራ ልዑክ በሮም እየተካሄደ ባለው የዓለም ምግብ ፎረም እየተሳተፈ ነው፡፡
የዓለም ምግብ ፎረም በጣልያን ሮም በፈረንጆቹ ጥቅምት 17 እስከ 21 ቀን 2022 በሚቆይ መድረክ በርካታ ተሳታፊዎች በተገኙበት ጤናማ ምግብ፣ ጤናማ ዓለም በሚል ጭብጥ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
በዚህ ጉባዔ ኢትዮጵያ እየተሳተፈች ሲሆን ፥ የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን የተመራ የኢትዮጵያ ተወካዮች በጉባኤው እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዓለም ግብርናና ምግብ ድርጅት በ2022 ባወጣው ሪፖርት በፈረንጆቹ 2021 በዓለም 828 ሚሊየን ህዝብ በረሃብ እየተጠቃ እንደሚገኝና 3 ነጥብ 2 ቢሊየን የዓለም ህዝብ ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ እያገኙ እንዳልሆነ አመላክቷል፡፡
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የ2030 ዘላቂ ልማት ግቦች በተለይም ረሀብን የማጥፋት ዕቅድ ያለበትን ሁኔታ ለመወያየትና አቅጣጫ ለማስቀመጥ፥ በአሁኑ ጊዜ በዓለም የተፈጠረውን የምግብ ፍጆታ ዋጋ መናር አስመልክቶ እየተወያዩ እንደሚገኙ ማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህ ጉባዔም የየሀገራቱ ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተወካዮች፣ የግብርና ምርምር፣ የግብዓት አምራች ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ በሮም ከሚገኘነው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያ ተወካዮች እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ፣ በቆላማ አካባቢ እየተካሄደ የሚገኘው አነስተኛ መስኖ ላይ የተመሰረተ የስንዴ ምርታማነትና ሌሎች ተሞክሮዎችን ለመድረኩ በማቅረብ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራትና ድጋፍ ለማግኘት የማመቻቸት ስራዎችን ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!