Fana: At a Speed of Life!

በመከላከያ ሠራዊት ስር በሚገኙ የትግራይ ከተሞች ሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ እየተሠራ ነው- መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰሞኑ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እጅ በገቡ የትግራይ ከተሞች ሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ አቅርቦት እና መሰረታዊ አገልግሎት ማስጀመርን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫውም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ከሰሞኑ የተወሰኑ ከተሞች መቆጣጠሩን አስታውቋል።

ሠራዊቱ በከተሞች አካባቢ ውጊያን ለማስወገድ ጥረት ማድረጉን የገለጸው መግለጫው÷ በዚህም ንጹሃን እንዳይጎዱ ያደረገው ከፍተኛ ጥረት ስኬታማ መሆኑ ነው የገለጸው፡፡

አሁን ላይም ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን ያለ ከተማ ውጊያ መቆጣጠሩን ያነሳው መግለጫው፥ ሠራዊቱ አንዳንዶች የአሸባሪውን ህወሓትን ፕሮፓጋንዳ በማስተጋባት ያነሱትን ሟርት ማስቀረት መቻሉንም ነው ያመላከተው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም በሠራዊቱ ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች ከሚመለከታቸው ረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡

ይህም የሽረ አውሮፕላን ማረፊያን ተጠቅሞ እርዳታ ማድረስን ይጨምራል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የሰብዓዊ ድጋፎች የሚቀርብባቸውን መንገዶች ለማስፋት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል።

መግለጫው ከሰሜን ጎንደር እስከ ሽረ ያለውን ጨምሮ ከኮምቦልቻ – ደሴ – ወልዲያ – ቆቦ – አላማጣ ያለውን መንገድ ለመክፈት በቅንጅት አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስቷል።

ይህንን ሥራ የሚያሣልጥ ኮሚቴ ከሚመለከታቸው አካላት ተወጣጥቶ ሥራ መጀመሩም ተጠቁሟል፡፡

እነዚህ ሥራዎች ቴክኒካዊ የሆኑ ጥናቶችን እና ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥራዎችን ይጨምራሉ ነው የተባለው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.