ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ከባድ የሙስና እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉ 3 የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዐቃቤ ሕግ በአዲስ አበባ ፖሊስ የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ሃላፊን ጨምሮ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ከባድ የሙስና እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽመዋል ባላቸው 3 የፖሊስ አባላት እና ግብረአበሮቻቸው ላይ ክስ መሰረተ፡፡
ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተውም 1ኛ ተከሳሽ ም/ኢንስፔክተር መንግስቱ ገብረሚካኤል አልባሞ (በአ/አ/ ፖሊስ የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ሃላፊ)፣2ኛ. ዋና ሳጅን ቦሴ ለምለሙ ሙልዬ (ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ)፣ 3ኛ. ሻለቃ ዮሀንስ አበበ (በመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰራዊት መኮንን) ፣ 4ኛ. አደም ሰይድ መሀመድ (በግል ስራ የሚተዳደር) እና 5ኛ. ረዳት ሳጅን ተማም አቡራይ ልካሳ (በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መከላከል አባል) ላይ ነው፡፡
የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያሳየው የግል ተበዳይ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከውጪ ለማስገባትና ጉዳይ ለማስፈጸም ከአንድ ድምጻዊ ሚያዚያ 6 ቀን 2014 ዓ.ም ውክልና ወስዳ አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 4 ሚሊየን 534 ሺህ 203 ብር የሆኑ እቃዎችን አስገብታለች፡፡
ተበዳይ እቃውን ካስገባች በኃላም 4ኛ ተከሳሽ የድምጻዊው ውክልና ስላለኝ ንብረቱን አስረክቢኝ በማለት የግል ተበዳይን ሲጠይቃት እሷም እቃውን ለማስገባት ለጉምሩክ የከፈለችውን 1 ሚሊየን 200 ሺህ ብር እና ስራውን የሰራችበትን 2 ሚሊየን ብር በድምሩ 3 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በቅድሚያ እንዲከፍላት ትጠይቃለች፡፡
4ኛ ተከሳሽም ጉዳዩን በሕጋዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ከ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር 3ኛ ተከሳሽ የመከላከያ ሰራዊት አባልነቱን በመጠቀም የወታደራዊ ደንብ ልብስ እንደለበሰ ካልተያዙት ግብረ አበሮቹ ጋር ወደ መኖሪያ ቤቷ በመሄድ በተበዳይዋ ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት ፈጽመዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በማሳሰር ብሎም ከታሰረችበት የፖሊስ ጣቢያ ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 10፡30 ሰዓት ሲሆን ወደ አየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ “ንብረቱን ካልመለስሽ ክሱን ወደ ሽብር ወንጀል እንቀይረዋለን እናሳይሻለን” በማለት ያስፈራሯታል፡፡
ቀጥሎም ከተበዳይ የግል ስልክ ላይ ንብረቱ ይገኝበታል ያሏቸውን ስልክ ቁጥሮች ከወሰዱ በኋላ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የሴት እስረኛ ማቆያ እንደሌለው እያወቁ ሆን ብለው ለሌላ አገልግሎት ከሚጠቀሙበት መብራት እና መኝታ ከሌለው፣ በሩ ከውስጥ ከማይዘጋ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ ባዶ ክፍል ውስጥ እንድታድር ያደርጋሉ፡፡
በዚያው ዕለት የአዳር ተረኛ ጥበቃ በመሆን ተመድቦ ሲሰራ የነበረው 5ኛ ተከሳሽ ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ የፖሊስ መለዮውን እንደለበሰና የጦር መሳሪያ እንደያዘ የግል ተበዳይ ያለችበትን ክፍል በር ከፍቶ በመግባት ‹‹ብትጮሂም ምንም አታመጪም፣ ማንም አይደርስልሽም፣ የግቢውን በር ቆልፌዋለሁ፣ ብቻዬን ነኝ፣ እጮሀለሁ ካልሽ በዚህ ክላሽ እመታሻለሁ›› በማለት የግል ተበዳይን በብርቱ ዛቻ በማስፈራራት መከላከል እንዳትችል በማድረግ አስገድዶ ደፍሯታል፡፡
ከደፈራት በኋላም በሩን ዘግቶ በመውጣት ከአንድ ሰዓት በኋላ ተመልሶ በመምጣት ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀመባት ሲሆን ÷ የግል ተበዳይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከተፈጸመባት በኋላም እዛው ክፍል ውስጥ ለ3 ቀን እንድታድር 1ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ በመስጠት፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ ንብረቱን ብትመልስ እንደሚሻላት በመዛት ንብረቱን አስቀምጦ የነበረው ግለሰብ በወንጀል ባልተጠረጠረበትና ክስ ባልቀረበበት ሁኔታ በማታለል ወንጀል እንደተጠረጠረ አስመስለው በ1ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ ሰጪነት የብርበራ ትእዛዝ አውጥተው በመኖሪያ ቤቱ ብርበራ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም ለጊዜው ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-56045 ኦ.ሮ የሆነ ዶልፊን መኪና እስከ ለሊቱ 6 ሰዓት በማቆም ጫና በመፍጠር፣ ከፍተኛ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመፈጸም 4ኛ ተከሳሽ ንብረቱን የተቀበለ በመሆኑ፣ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ እና 4 ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል 5ኛ ተከሳሽ ደግሞ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
በተጨማሪም 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሽ ንብረቱ እሱ ጋር ይሆናል ብለው ያሰቡትን አቶ ቢኒያም ጳውሎስን ንብረቱን እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ሲዝቱና ሲያስፈራሩት ቆይተው በሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ሰዓቱ በውል ባልታወቀ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወንድማማቾች ስጋ ቤት አካባቢ 3ኛ ተከሳሽ ለጊዜው ካልታወቁ የመከላከያና የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ 5 ሰዎችና ሌሎች 2 ግለሰቦች ጋር በመሆን የግል ተበዳይ አቶ ቢኒያም ጳውሎስን ለመያዝ በመኪና በማባረር አራት ጥይቶችን በመተኮስ ከያዙት በኋላ 3ኛ ተከሳሽና ለጊዜው ያልተያዙት ተጠርጣሪዎች በመሳሪያ እየደበደቡ መኪና ውስጥ አስገብተው አይኑን በጨርቅ አስረው ወደ ጎልፍ ክለብ ወስደውታል፡፡
በዚህም ከሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በሕገ ወጥ መንገድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ለ15 ቀናት አስረው ካቆዩት በኋላ ንብረቱን በሃይል ስላስመለሱ የግል ተበዳይን የለቀቁት በመሆኑ ሁለቱም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ህግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ጥቅምት 8 ቀን 2015 ቀን ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾች የክሱ ማመልከቻ ደርሷቸው ከጠበቃ ጋር ለመቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጣቸው መሆኑንም ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡