Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ባንክ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለሚጠቁሙ ወሮታ የሚከፈልበትን መመሪያ በሚመለከት ማብራሪያ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9 ፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለሚጠቁሙ ወሮታ የሚከፈልበትን መመሪያ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ባንኩ በቅርቡ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለሚጠቁሙ ዜጎች ወሮታ እከፍላለሁ ማለቱን ተከትሎ ነው ስለአጠቃላይ መመሪያው ዛሬ ማብራሪያ የሰጠው፡፡

አራት ህገወጥ ጉዳዮች ላይ ህብረተሰቡ ጥቆማ እንዲያደርግና ጥቆማ ለሚያደርጉ ዜጎችም ወሮታ እንደሚከፍል ማስታወቁም ይታወሳል፡፡

በዚህም መሰረት፡-

  1. ከተፈቀደ በላይ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ገንዘብ ማከማቸት

2.ሀሰተኛ የገንዘብ ህትመት መፈፀም

  1. የወርቅ ክምችት
  2. ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ያለፈቃድ ማስተላለፍ በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ ዜጎች ጥቆማ እንዲሰጡ እና ዜጎች ለሚሰጡት ጥቆማ ወሮታ እንደሚከፈላቸው ተገልጿል፡፡

በባንክ ከተፈቀደው በላይ የገንዘብ መጠን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችን ለጠቆሙ ከተያዘው ገንዘብ 15 በመቶ፣ የውጭ ሀገር ገንዘብ ዝውውር ለሚጠቁሙ 15 በመቶ፣ ሕገወጥ ሐዋላን ለሚጠቁሙ 25 ሺህ ብር ወሮታ እንደሚከፍል ጠቁሟል፡፡

ለግለሰቦች በቀን ከ100 ሺህ ብር በላይ መያዝ፣ ለተቋማትም በቀን ከ200 ሺህ ብር በላይ መያዝ የተከለከለ ነው ተብሏል።

ይህን መመሪያ የተላለፈን ግለሰብ ወይም ተቋም ለጠቆመ ምስጢራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ ወሮታው ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል።

ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ግለሰብም በከባድ የኢኮኖሚ ወንጀል እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ነው የተመላከተው።

ጠቋሚዎች በስልክ ቁጥር 0118133960፣ በኢ.ሜል አድራሻ tikoma@nbe.et፣ በፋክስ ቁጥር 0115514366 እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፖ.ሣ.ቁጥር 5550 ላይ ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል ባንኩ አስታውቋል።

በፀጋዬ ወንደወሰን

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.