ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የመንግሥት የሰላም እጆች አይታጠፉም- አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የመንግሥት የሰላም እጆች መቼም ቢሆን እንደማይታጠፉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት የሰላም በሮችን ክፍት አድርጎ እየጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት የዜጎቿ ትብብር፣ የሁሉም አካላት የሰላም ቁርጠኝነትና ለምክክር ዝግጁ መሆኑ አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በተለይም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት የመንግሥት ቁርጠኝነት እንዳለ መሆኑን ጠቁመው÷ በጥፋት መቀጠል ከፈለጉት አካላት ግን ተቃራኒ ሐሳቦች አሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ ከምንጊዜውም በላይ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እየሠራ መሆኑን ገልጸው÷ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የመንግሥት የሰላም እጆች አይታጠፉም ብለዋል፡፡
በአንጻሩ መርህን ባልተከተለ አካሄድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ የውጭ ኃይሎች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ አደም÷ በውስጥ ያሉ የሽብር ቡድኖችም በጥፋት እንቅስቃሴያቸው ቀጥለውበታል ነው ያሉት፡፡