Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ከአሸባሪው ቡድን ነጻ በወጡ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ በተሣለጠ መንገድ እንዲደርስ በቂ ዝግጅት ተደርጓል – ለሰብዓዊ ድጋፍ የተዋቀረው ኮሚቴ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ከአሸባሪው ህወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ በተሣለጠ መንገድ እንዲደርስ በቂ ዝግጅት መደረጉን ለሰብዓዊ ድጋፍ የተዋቀረው ኮሚቴ አስታወቀ።

የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦትን ለማሳለጥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል።

የኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መከላከያ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታውን በተሣለጠ መልኩ ለማድረስ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንና ወደ ተግባር መግባቱንም ገልፀዋል።

ኮሚቴው ዝግጅቱን አስመልክቶ ባደረገው ውይይት ከአሸባሪው ነጻ በወጡ የትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ባለድርሻ አካላት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አረጋግጧል።

የሽረ አውሮፕላን ማረፊያን ተጠቅሞ ዕርዳታ ማድረስን እንደሚጨምር የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትርና የኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።

ሰብዓዊ ዕርዳታን በተቀናጀ፣ በተፋጠነና በተሣለጠ መንገድ ማድረስ የመንግስት ፅኑ አቋም እንደሆነም ገልፀዋል።

ለዚህም ኮሚቴው በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ የሚከናወኑ ተግባራትን ለይቶ በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቅሰው፥ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የመንግስት መዋቅሩን መልሶ በማደራጀት የተቀናጀ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።

መንግስት ያስቀመጠው አቅጣጫ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ያመለከቱት የኮሚቴው አባላት፥ ውሳኔውን ለመተግበር በየዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም አስረድተዋል።

በዚህም ከአሸባሪው ህወሓት ነፃ በወጡ አካባቢዎች የእርዳታ አቅርቦቱ ሳይስተጓጎል ማድረስ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ በቅንጅት እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

መንግሥት ከሰብአዊ የእርዳታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሰብአዊ ዕርዳታ የሚደርስባቸውን መንገዶች እያስፋፋ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በትናንትናው እለት መግለፁ ይታወቃል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.