Fana: At a Speed of Life!

24ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 24ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ በሐዋሳ ከተማ ተካሄደ፡፡

በጉባኤው የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች እና በየደረጃው ያሉ የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አቶ ደስታ ሌዳሞ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በጤናው ዘርፍ የመጣው ለውጥ ኢትዮጵያ በዘርፉ አንገቷን ቀና እንድታደርግ አስችሏል ብለዋል፡፡

በዘርፉ የተገኘው ውጤትም የመንግሥት ጠንካራ ፖሊሲና አፈፃፀም ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የጤና ፖሊሲውን በማስፈፀም ረገድ በዘርፉ ያሉ መሪዎች ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመው÷ ዓለም በተፈተነች ጊዜ ኢትዮጵያ ፈተናውን እንድትመክት ማስቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

የኮቪድ ወረርሺኝ እንደ ሌሎቹ ሀገራት የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ፈተናውን ለማለፍ በተሠራው ጠንካራ ሥራ ተጽዕኖውን መቋቋም እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

ጉባዔው “ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ” በሚል መሪ ቃል እስከ ነገ ድረስ ይካሄዳል።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የገጠሙን የጦርነት፣ የኮቪድ ወረርሺኝና ሌሎች ተግዳሮቶች የጤናው ዘርፍ ላይ ፈተና ቢፈጥሩም÷ ፍትሐዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ከማድረስ አኳያ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ማድረስ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የ2014ዓ.ም አፈፃፀም ዕድገት የታየበት መሆኑን ጠቁመው÷ በተያዘው በጀት ዓመት መልካም ተሞክሮችን በማስቀጠል ችግሮች ተፈትተው ይበልጥ የተሻለና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማድረስ ቀጣይ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

የመድኃኒት አቅርቦትን ማሻሻል፣ ግጭትና በጦርነት የተጎዱ ጤና ተቋማትን በመገንባት እና በመጠገን ወደ ሥራ ማስገባት ትኩረት የሚሰጠው ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ትኩረት ያደረገ ስራ እንደሚሠራም ገልፀዋል።

በታሪኩ ለገሰ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.