ሞስኮ በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ለመጠቃለል በወሰኑት ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ባለፈው ወር በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ለመጠቃለል በወሰኑት የዶኔስክ ፣ ሉሃንስክ ፣ ኬርሰን እና ዛፖሮዢ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች፡፡
ዩክሬን ህዝበ ውሳኔውን ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ ÷ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ሀገራቸውን ከሚሰነዘርባት ጥቃት ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ያደረጓቸውን በርካታ የፖሊሲ ለውጦች የሚገልጹ ሰነዶችን መፈረማቸውንም በብሔራዊ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ዩክሬን በሩሲያ ላይ የሽብር ተግባር እየፈጸመች ነው ሲሉም ኪየቭን ኮንነዋል፡፡
ዩክሬን መሠረተ ልማቶችን ወደ ማውደም እና ባለሥልጣናትን ወደ መግደል የወረደ እርምጃ ውስጥ ገብታለችም ነው ያሉት ፑቲን።
ቀደም ሲል ዩክሬን በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ፕሬዚዳንት ፑቲን አስታውሰዋል፡፡
በተጨማሪም ዩክሬን ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ፣ ሰፊ የትራንስፖርት እና የኃይል አቅርቦት አገልግሎቶች በሚሰጡባቸው ተቋማት ላይ በርካታ የታቀዱ የሽብር ጥቃቶች ከመፈጸሟ በፊት የሩሲያ ደኅንነት አካላት ጥቃቶቹን ማክሸፍ መቻላቸውንም አመላክተዋል።
ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን በክሪሚያ ፣ ሴቫስቶፖል ፣ ክራስኖዳር፣ ቤልጎሮድ፣ ብሪያንስክ፣ ቮሮኔዝ፣ ኩርስክ እና ሮስቶቭ ግዛቶች እና ከተሞች መካከለኛ የሚባል የደኅንነት እና ጸጥታ ቁጥጥር እንዲካሄድ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡