Fana: At a Speed of Life!

ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትና ጫና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በብራሰልስ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትና ጫና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በብራሰልስ ተካሄደ፡፡

በአውሮፓ ኮሚሽን ፊት ለፊት በሚገኘው ሹማን አደባባይ እየተካሄደ በሚገኘው ሰልፍ÷ በአውሮፓ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል።

ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስና ጀርመን ዳያስፖራዎቹ ከመጡባቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

የሰልፉ ዓላማ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት በመቃወም ነባራዊ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንደሆነ ከ‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ’ የብራሰልስ አስተባባሪዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሰልፈኞቹ አንዳንድ ሀገራትና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንዲያቆሙና እጃቸውን እንዲያነሱ የሚያስገነዝቡ መፈክሮች እያሰሙ ይገኛል።

የሰልፉ አስተባባሪዎች የአውሮፓ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ላይ እየደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ደብዳቤ ለኮሚሽኑ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ አቅርበዋል።

ሰላማዊ ሰልፉ የሚከናወንበት ሹማን አደባባይ ከኮሚሽኑ በተጨማሪ የቤልጂየም ፓርላማ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ እና ሌሎችም ትላልቅ የመንግስት ተቋማት የሚገኙበት ነው።

‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ’ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በማስተባበር በዲጂታል ምህዳሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በትዊተር የተለያዩ መልዕክቶችን በመቅረጽ ዘመቻ እያካሄደ እንደሚገኝ ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.