Fana: At a Speed of Life!

የምዕራባውያንን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ህዝባዊ ሰልፍ የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ”ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል የምዕራባውያንን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ህዝባዊ ሰልፍ የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ ነው።

ህዝባዊ ሰልፉን የሙያ ማህበራት፣ የሲቪክ ማህበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ያዘጋጁት ነው ተብሏል፡፡

የሰልፉ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅና ለአገሪቱ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር በሁሉም መስክ ከመንግስት ጎን መቆማችንን ለማረጋገጥ ነው ሲሉ የሰልፉ አዘጋጆች ገልፀዋል፡፡

በሰላማዊ ሰልፉ ምዕራባውያን በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የያዙትን የተለሳለሰ አቋም እና በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ጫና የሚቃወሙ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

የምዕራባውያን ሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያስተላልፉትን የተሳሳተ መልዕክት የሚቃወሙ መልዕክቶች በሰላማዊ ሰልፉ ይተላለፋሉም ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም አሸባሪው የህወሓት ቡድን የቀረበለትን የሠላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ለ3ኛ ጊዜ የጀመረውን አስገዳጅ ጦርነት ለመቀልበስና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እያደረገ ላለው ተጋድሎ በሁለንተናዊ ድጋፍ ህዝቡ ደጀንነቱን የሚያሳይበት ሰልፍ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የድጋፍ ሠልፉ የፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 12 ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በነቂስ በመውጣት በተዘጋጀው ሰልፍ ላይ በመሳተፍ በምዕራባውያን ሀገራት እየደረሰ ያለውን ጫና እንዲያወግዙ እና ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ቀርቧል።

ህዝባዊ ሰልፉ በመላው ኢትዮጵያ እንደሚካሄድም ነው የተገለጸው፡፡

በምንተስኖት ሙሉጌታ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.