የሀገር ውስጥ ዜና

ቦርዱ በደቡብ ክልል ለሚያካሂደው ህዝበ ውሳኔ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ

By Alemayehu Geremew

October 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል የሚገኙ ሥድስት ዞኖች እና አምሥት ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያካሂደው ህዝበ ውሳኔ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈፀም ከጠየቀው 541 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ውስጥ 410 ነጥብ 1 ሚሊየን ብርሩ እንደተፈቀደለት ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ በዞኞቹ እና ልዩ ወረዳዎች 36 የህዝበ ውሳኔ ጽኅፈት ቤቶችን ለመክፈት በመስከረም ወር ለአካባቢው አስተዳደር አካላት ቢያሳውቅም የጋሞ ዞን ብቻ ምላሽ መሥጠቱን እና በአርባ ምንጭ ከተማ የህዝበ ውሳኔ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት መክፈቱን አንስተዋል።

ህዝበ ውሳኔው ጥር 29 ቀን 2015 እንደሚካሄድና ቀድሞ ይፋ የተደረገው የህዝበ ውሳኔው አፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ በቦርዱ በትናትናው ዕለት መጽደቁን ጠቁመዋል ።

በጊዜ ሰሌዳ ላይ በገዢው ፖርቲ ከተያዘው በአጠረ ጊዜ ውስጥ እንዲከናወን ጥያቄ ሲቀርብ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ የይዘግይ ጥያቄ ቢነሳም ቦርዱ በሁለቱም በኩል አሳማኝ ምክንያት ባለመቅረቡ የጊዜ ሰሌዳውን አጽድቆታል ነው ያሉት ሰብሳቢዋ።

የህዝበ ውሳኔ ከሚያስፈልጉት 18 ሺህ 750 ውስጥ የሀገር አቀፍ ምርጫውን ያስፈፀሙ 9 ሺህ አስፈፃሚዎች መዘጋጀታቸውንም አንስተዋል፡፡

ተጨማሪ 9 ሺህ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለማካተትም በበይነ መረብ እንዲመዘገቡ ቢርዱ ማስታወቂያ እንደሚያወጣ አብራርተዋል፡፡

በበላይ ተስፋዬ