Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ ክልሎች የከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ክልሎች “በደም የተከበረ በላብ የታሰረ” በሚል መሪ ሀሳብ የከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡

ለሁለት ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድድር አቶ አወል አርባ ፥ በደም የተከፈለውን መስዋዕትነት በላብ ካልታሰረና ካልጸና ሉዓላዊነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸው አይቀርም ብለዋል።

“በክልሉ ከዚህ በፊት የስንዴ ምርት ፣ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር፣ የክልሉን ገቢ ለማሻሻል፣ ለመከላከያ ሠራዊታችን ደጀን በመሆን የተከናወኑ ሥራዎች አበራታች ነበሩም” ነው ያሉት፡፡

የክልሉ አመራርና ህዝቡ የተደራጀ ሌብነትን አምርሮ መታገልና ማረም እንደሚገባ ገልጸው ፥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ሌብነት ይቅር የማይባሉ ጥፋቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

የአፋር ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢሴ አደም በበኩላቸው፥ “የችግሮቻችንን ምንጭ በመለየት እና በመረባረብ በላብ የታሠረ ተግባር በመፈጸም ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት በየደረጃው ራስን በምግብ መቻል እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባናል” ነው ያሉት።

በተመሳሳይ ሶማሌ ክልል በተካሄደው ውይይት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን፥ “የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሚከፈለው የደም መስዋዕትነት ባሻገር ቀጣይነት ያለው ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማረጋገጥ የሀገር ክብርና ነፃነት በላባችን እንዲጸና ማድረግ ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር፣ የክልሉን ገቢ ለማሻሻል፣ ለመከላከያ ሠራዊታችን ደጀን በመሆን የተከናወኑ ሥራዎች አበራታች እንደነበሩ አስታውቀው ፥ ይህም ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

የአሸባሪውን የአልሸባብ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ትልቅ ድሎችን ማስመዝገብ መቻሉ የተገለፀ ሲሆን ፥ ይህንኑ ድል በሁሉም የልማት መስኮች መደገም አለበት ነው የተባለው፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የከፍተኛ አመራሮች የሚያካሂዱት የውይይት መድረክ ዘላቂ ሰላምና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትኩረት አድርጓል ተብሏል።

በተለይም የለውጥ አመራሩ ወደ ኃላፊነት ከመጣ ወዲህ ባሉት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮችንና የተመዘገቡ ስኬቶችን በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ግንዛቤ ለመፍጠርና ለሀገር ሠላምና ዕድገት ስኬት አመራሩ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ለማድረግ ያለመ ነው።

ምንጭ፡- የክልሎቹ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮዎች

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.