Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት የኢትዮ ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሥራ ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ኃይል ማስተላለፍ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

ህብረተሰቡ ከኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ንክኪ እንዲርቅም ተቋሙ ጠይቋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክብሮም ካህሳይ የተመራ ቡድን ከወላይታ ዞን አስተዳዳሪና የመምሪያ ኃላፊዎች ጋር እንዲሁም ከጋሞ ዞን አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ መስመሩ ለሁለቱ ሀገራት የኃይል ትስስር እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡም መስመሩ ኃይል ያልተለቀቀበት መስሎት በመዘናጋት ጉዳት እንዳይደርስበት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዲሰራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በተመሳሳይ በፕሮጀክቱ ሥራ መጀመር ዙሪያ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት መደረጉንከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ፕሮጀክቱ በሚያልፍበት የቦረና ዞን እንስሳትን የሚጠብቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢንሱሌተሮችን ለጨዋታ በሚል እየሰበሩ በመሆናቸው ድርጊቱን ለማስቆም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር እንዲሰራ ተጠይቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.