በደቡብ ክልል በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ለተፈናቀሉ ወገኖች የ320 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በደቡብ ክልል በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም የ320 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ድጋፉን ለደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ አስረክበዋል።
ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት÷ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ችግሮች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ ነው፡፡
እንዲሁም በሰሜኑ በጦርነት ምክንያት የሽብር ቡድኑ ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶች በእልህ እና በቁጭት እየተገነቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የ18 ተቋማት ግንባታ መካሄዱን ጠቁመው÷ ይህም በጨለማ ውስጥ ብርሃን እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው÷ ሚኒስቴሩ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
በሰሜኑ ጦርነት የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መልሶ በማቋቋም ረገድ የክልሉ መንግሥት አጋርነቱን ሲያሳይ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በክልሉ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ችግሮች ተፈናቅለው የነበሩ 123 ሺህ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውን ገልጸው÷ አሁን ተፈናቅለው የሚገኙ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!