Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በ90ኛው በለም ዓቀፍ የፖሊስ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተሳተፈች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በህንድ ኒውዴልሂ ከተማ በተካሄደው 90ኛው ዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተሳትፋለች።

ጉባዔው በፈረንጆቹ ከጥቅምት 18 እስከ 21 ቀን 2022 የተካሄደ ሲሆን ÷ የ188 አባል ሀገራት ፖሊስ አዛዦች፣ ሚኒስትሮች እና የተለያዩ ከፖሊስ ጋር በአጋርነት የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ ልዑካን ቡድንም በጉባዔው ተሳትፏል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከዓለም ዓቀፍ የፖሊስ ድርጅት ፕሬዚዳንት ሜጀር ጀነራል አህመድ ናሲር አል-ረኢሲ፣ ከቀጠና ቢሮ ኃላፊዎች እና ከአፍሪካ የኢንተርፖል ተጠሪዎች ጋርም የጎንዮሽ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ከዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ፕሬዚዳንት ሜጀር ጀነራል አህመድ ናሲር አል-ረኢሲ ጋር ÷ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት የምታደርገው አስተዋፅዖ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጀመረውን የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰው ሃይል አቅም ግንባታ፣ የፎረንሲክ እና የሳይበር ወንጀል ምርመራን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከኢንተርፖል ጋር በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መወያየታቨቸውም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ኮሚከናሚቢያ ሪፐብሊክ ፖሊስ ሌተናል ጄኔራል ዮሴፍ ሺሙዌላኦ ሺኮንጎ ጋር የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትብብር በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በተመሳሳይ ከጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ኃይል ልዑካን ቡድን ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሁለቱ ፖሊስ ተቋማት እየተሰሩ ባሉት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ከምስራቅ አፍሪካ የዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት ኃላፊ ሚስተር ጌዲዮን ኪሚሉ፣ ከወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዚዳንት፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ዣን ባሎንጋንዲ እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት ፖሊስ ሃላፊዎች ጋር መምከራቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በተመለከተ ተፈላጊዎችን አሳልፎ ለሀገራት በመስጠት ረገድ በትብብር ከመስራት አንፃርም የተሻለ ተሳትፎ እንዳላት መጠቀሷ ተገልጿል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.