ነገ በመዲናዋ ለሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ የሚዘጉ መንገዶች ይፋ ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በነገው ዕለት በመስቀል አደባባይ የሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አስታወቀ።
“ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምፄን አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ከተሞች ጥቅምት 12 እና 13 ቀን 2015 ዓ.ም የድጋፍ ሰልፍ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
ህዝባዊ ሰልፉ መንግስት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት ለማስከበር የሚያደርገውን የመከላከል እርምጃ የሚደግፍ እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ነው ተብሏል፡፡
የድጋፍ ሰልፉ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ የጋራ ግብረ ሃይሉ አስታውቋል።
የድጋፍ ሰልፉ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በዚህ መሠረትም ፡-
- ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከኤድናሞል በአትላሳ ወደ ካዛንቺስ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል አደባባይ ላይ፣
- ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ አራተኛ ክፍለጦር፣
- ከጎፋ በአዲሱ መንገድ ወደ ለገሃር ለሚመጡ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን መስቀለኛ ላይ፣
- ከቡልጋሪያ በሜክሲኮ አደባባይ ወደ ለገሃር የሚሄዱ ለገሀር፣
- ከሳር ቤት ወደ ሜክሲኮ አደባባይ እንዲሁም ከጦር ኃይሎች በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወደ ለገሃር የሚወስደው ሜክሲኮ አደባባይ፣
- ከተክለ ሃይማኖት በጎማ ቁጠባ ወደ ለገሃር ሰንጋተራ 40/60 ኮንደሚንየም አካባቢ፣
- ከጌጃ ሰፈር ፣ በአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚሄዱ አሽከርካሪዎች ጎማ ቁጠባ አካባቢ፣
- ከመርካቶ በተክለ ሃይማኖት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሜትሮሎጂ በር ላይ፣
- ከራስ ቴአትር በጎላ ሚካኤል ውስጥ ለውስጥ ጎላ ሚካኤል መስቀለኛ መንገድ ላይ፣
- ከተክለ ሃይማኖት ጥቁር አንበሳ ኢሚግሬሽን ጥቁር አንበሳ ሼል አጠገብ፣
- ከፒያሳ በቸርችል ጎዳና ለገሃር ቴዎድሮስ አደባባይ፣
- በአሮጌው ቄራ ፍል ውሃ ንግድ ማተሚያ ቤት አካባቢ፣
- ከካዛቺስ ወደ ሂልተን ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ፣
- ከአዋሬ በካዛንቺስ ወደ ፍል ውሃ የሚወስደው መንገድ ፍል ውሃ አካባቢ፣ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡
ስለሆነም አሽከርካሪዎች ይህንኑ አውቀው አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ እና በተገለፁት መንገዶች ላይ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ እንዲሁም ከአርብ ምሽት ጀምሮ ተሽከርካሪ ማሳደር ፍፁም ክልክል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ህብረተሰቡም የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘት ሆነ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት መረጃ ለመስጠት 991 ወይም 816 ነፃ የስልክ መስመሮችን እና 0111 -11- 01 -11፣ 0111- 26- 43- 59 እንዲሁም በ0111- 01- 02- 97፣ መጠቀም እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡