የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በጋዝ ዋጋ ማሻሻያ ላይ ሳይስማሙ መቅረታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በጋዝ ዋጋ ማሻሻያ ላይ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ መቅረታቸው ተገልጿል፡፡
በአንጻሩ አባል ሀገራቱ ለኃይል ቀውሱ የጋራ መፍትሄዎችን ለመፈለግ ፈቃደኞች መሆናቸው ነው የተመላከተው፡፡
የአውሮፓ ህብረት ም/ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል በብራሰልስ ከተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ በኃላ በሰጡት መግለጫ ÷ በህብረቱ አባል ሀገራት ዘንድ የነዳጅ ዋጋ ቅነሳ፣ የአቅርቦት ደህንነት ማረጋገጥ እና ፍላጎትን መቀነስ የሚሉ ሶስት ግቦችን ለማሳካት የጋራ ቁርጠኝነት አለ።
የአውሮፓ ህብረት በጉባኤው የኃይል ቀውሱን ለማቃለል እርምጃ እንደሚወስድ እና በቅርቡም ውጤት እንደሚኖር ቃል መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
በጋዝ የዋጋ ማሻሻያ ላይ ከስምምነት መድረስ ያልቻሉት የአውሮፓ ህብረት መሪዎች÷ ኮሚሽኑ በተፈጥሮ ጋዝ ግብይት ላይ ጊዜያዊ የዋጋ ማሻሻያ እንዲፈጥር እና ከልክ ያለፈ የዋጋ ንረትን በፍጥነት ገደብ እንዲያበጅለት ጠይቀዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ህብረት ኢነርጂ ሚኒስትሮች በችግሩ ላይ መፍትሄ ለማበጀት በሚቀጥለው ሳምንት ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አርቲ ዘግቧል።
በፈረንጆቹ መስከረም መገባደጃ ላይ የሩሲያ ጋዝን በጀርመን በኩል ለአውሮፓ ደንበኞች የሚያደርሱት የኖርድ ስትሪም የጋዝ መስመሮች ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ይታወሳል፡፡